በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነቡት ሎጅና ሪዞርቶች በክልሎች በኩል የስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው መደረጉ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነቡት ሎጅና ሪዞርቶች በክልሎች በኩል የስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው መደረጉ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነቡት ሎጅና ሪዞርቶች በክልሎች በኩል የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው መደረጉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠትና ልምድን ለማካፈል እንደሚያስችል ተገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን ከፈረሙት መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በክልሉ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አመካኝነት ከፍተኛ ጥራትን ያሟሉ እና የአካባቢውን የመስህብ ገፅታ የቀየሩ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመነሻ እስከ መዳረሻ የተሳሰረ የጎብኚዎች የጉዞ መስመርን ያሟሉ አንደኛውን የመስህብ ስፍራ ከሌላው የሚያገናኙ ናቸው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተፈረመው ስምምነትም የቱሪዝም አገልግሎትን በላቀ ሁኔታ ለማሳለጥ፣ በየክልሎቹ ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ልምድ እንዲቀስሙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ በጥራት ተገንብተው የተጠናቀቁ መሆናቸው ለሌሎች ፕሮጀክቶች ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት፣ የአካባቢውን ገፅታ በማስዋብ እና የአገልግሎት ልህቀት ማዕከል በመሆን ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
ለክልሎችም ከዚህ ልምድ በመውሰድ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለመገንባት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
አገልግሎት የጀመሩ መዳረሻዎች በክልሎች ባለቤትነት የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው መደረጉ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎትን በክልሎች ለማስፋፋት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፥ ቱሪዝምና የአየር ትራንስፖርት የተቆራኙ መሆናቸውን ገልጸው አየር መንገዱ ቱሪዝምን በኢትዮጵያ ለማነቃቃት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴልም ደረጃውን የጠበቀ የመስተንግዶ አገልግሎትን ለጎብኚዎች በመስጠት ምቹ የቆይታ ስፍራ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይህን አገልግሎቱን ወደ ክልሎች ለማስፋፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው የዛሬው ስምምነትም የረጅም ጊዜ የአየር መንገዱን ህልም ያሳካ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ መልካም እድልን ከኃላፊነት ጋር አስተሳስሮ የሰጠ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት በመስጠት ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜያቸው የተመቸ እንዲሆን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
በአዲስ ዕይታ ለውጤት የበቁት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ኢኮኖሚውን በማነቃቃት፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎትን የላቀ በማድረግ ተምሳሌታዊ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል የተረከባቸው ፕሮጀክቶችም የአገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና በአካባቢው ላሉ አገልግሎት ሰጪዎች ምሳሌ መሆን የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም የሀገርን የቱሪዝምና ሆቴል አገልግሎት ጥራት ከፍ ለማድረግና ገፅታ ለመገንባት ትልቅ ዕድል እንደሆነም ነው ሚኒስትሯ ያነሱት።