በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ ሰምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ ሰምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሰምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የቱሪዝም ልማትን ለማስፋፋት የሚያግዘ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አመካኝነት የሀላላ ኬላ ሪዞርት፣ የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም፣ እንዲሁም የጎርጎራ ፕሮጀክቶች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡
በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተከናወነው መርሃ ግብር እነዚህ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች የተላለፉ ሲሆን፤ ክልሎችም በኢትዮጵያ አየር መንግድ ግሩፕ ስር የሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል ስር ሎጅ እና ሪዞርቶቹን እንዲያስተድር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሃይ ጳውሎስ በዚሁ ጊዜ፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በየአከባቢው ያሉንን እምቅ አቅሞች መለየትና መጠቀም እንደሚቻል ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቶቹ የተመዘገበው ውጤታማነትም ሌሎች የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ እድል የፈጠረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የዛሬው ስምምነትም በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል አመካኝነት በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ አገልግሎት በመስጠት የቱሪዝም ዘርፍን ለማነቃቃት አንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
በሎጅና ሪዞርቶቹ የሚሰጠው አገልግሎት በቀጣይ ውጤታማ እንዲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
ክልሎች በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ያሳዩትን ትብብር አሁንም አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ህዝብን በልማት በማሳተፍ ረገድ ትልቅ ልምድ የሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ከማድርግ ባሻገር የትኛውንም ፕሮጀክት በጥራትና በፍጥነት ማከናወን እንደሚቻል ትምህርት የተወሰደባቸው መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡
የዛሬው ስምምነትም በመስኩ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡