ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከግንቦት 01 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ይካሔዳል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከግንቦት 01 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኤክስፖው የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም በማሳየት 3 ቢሊየን ብር የሚገመት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሔደው ኤክስፖ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ፣ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን ጨምሮ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል።

የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖውን ለማካሄድ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት መደረጉን እንዲሁ። 

በኤክስፖው ላይ 80 አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም 120 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። 

መድረኩ የኢንዱስትሪውን አቅም በማሳየት የገበያ ዕድልና ትስስር እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

በኤክስፖ ላይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃጨርቅ ፣ የምግብና የእንጨት ስራ ውጤቶች ፣ ኬሚካልና አውቶሞቢልን ጨምሮ ልዩ ልዩ ምርቶች እንደሚቀርቡ አንስተዋል። 

በተጨማሪ የፖናል ውይይት ከማካሔድ ባለፈ በወጪና ተኪ ምርት ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አካላት ዕውቅና እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ መፍታት ፣ ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማስቻል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸው ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም