በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን ለማረጋገጥ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶች እንዲጎለብቱ እንሰራለን - ወጣት ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና እድገትን ለማረጋገጥ የጋራ ሀገራዊ ገዢ ትርክቶች እንዲጎለብቱ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣት ምሁራን ገለጹ።

የተዛቡ ነጠላ ትርክቶች የኢትዮጵያውያን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ላይ ችግር በመፍጠር፣ የታሰበው ሰላምና እድገት እንዳይረጋገጥ ስጋት ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

መንግስትም ለኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሻገር እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን ለማፅናት አሰባሳቢ የጋራ ትርክት መፍጠር ወሳኝ ነው በሚል አቋም እየሰራ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣት ምሁራን በሀገሪቱ ተጨባጭ ሰላምን ለመገንባት፣ አብሮነትን ለማጠናከርና እድገትን ለማረጋገጥ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እንዳልካቸው አበራ ጠንካራ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወጣቶች አይተኬ ሚና እንዳላቸው ጠቅሷል።

ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት አልተጠናቀቀም ያለው ወጣቱ ምሁር ከዚህ አኳያ ወጣቶች ትልቅ የቤት ስራ እንዳለባቸው ተናግሯል።

በተለይም የህዝብን አንድነት ከሚሸረሽሩ ጉዳዮች በመራቅ ሁሉም በሀገሩ ጉዳይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ እና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መስራት አለብን ነው ያለው።

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርቷ ቃልኪዳን ደረጄ በበኩሏ የሀገርን እድገት ወደ ኋላ የሚጎትቱ እና የህዝቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ የፅንፈኝነት ትርክቶች መኖራቸውን ገልጻለች።


 

በመሆኑም ወጣት ምሁራን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጎልበት እና ትውልዱን በመልካም ሰብዕና የማነፅ ሙያዊ ኃላፊነት አለብን ነው ያለችው።

ወጣቱ ትውልድ ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ከፋፋይ አጀንዳዎች እና ከሀሰተኛ መረጃዎች መራቅ እንደሚገባው ያነሳው ደግሞ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን አብዱ ሀንፍሬ ነው።


 

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ካሉ ፈተናዎች እንድትወጣ የጋራ ሀገራዊ ትርክት መገንባት ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ነው ወጣት ምሁራኑ የገለጹት።

ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ መንግስት የጀመራቸው ስራዎች ለጋራ ገዥ ትርክት ግንባታ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥሩ አንስተዋል።

መንግስት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቶችን ያሳተፉ ውይይቶችንና የግንዛቤ መድረኮችን በማስፋት ወጣቶች ስለ አሰባሳቢ ትርክቶች በአግባቡ እንዲረዱ የማድረግ ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም