የኢትዮጵያን የአቬዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና በዘርፉ አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ተደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአቬዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና በዘርፉ አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ተደረጉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የአቬዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና በዘርፉ አብሮ ለመስራት የሚያችሉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ተደርገዋል።
ውይይቶቹ በዶሜኒካ ሪፐብሊክ በመካሄድ ላይ ከሚገኘው የዓለም አቀፍ የአቬዬሽን ድርጅት (ICAO) ሲምፖዚየም ጎን ለጎን ነው።
በሲምፖዚየሙ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የአቬዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀኃፊን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማትና ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር የኢትዮጵያን የአቬዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ ውይይቶቹ የኢትዮጵያን በአቭዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል በሰው ኃይል ስልጠና፣ በዲጂታላይዜሽን፣ የአየር ናቪጌሽን ቁጥጥር በማዘመን፣ የአውሮፕላን አካላትን ምርት በኢትዮጵያ በማስፋፋት እንዲሁም በአፍሪካ የአየር አገልግሎት ትስስር ለማጠናከር መምከራቸውን ገልጸዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሁለትዮሽ ውይይቶቹ ከካናዳ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ከሲንጋፖር እና ከሴራልዮን የትራንስፖርትና አቬዬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር ማድረጋቸውንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።