የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።
አዳማ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቷል።
ክለቡ በ34 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ በያዘው ኢትዮጵያ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ በሊጉ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም፤ በአራቱ ሽንፈት ሲያስተናግድ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።
በዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚሰለጥነው ሻሸመኔ ከተማ በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኛል።
ባህር ዳር ከነማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም፤ በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።
በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በ37 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ 33 ተመሳሳይ ነጥብ በመያዝ በፋሲል ከነማ በግብ ክፍያ ተበልጦ 8ኛ ደረጃን ይዟል።
ባህርዳር ከነማና ድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከነማ 2 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ መድን ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከቀኑ 9 ሰዓት እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የ23ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች እስከ ሚያዚያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪሚየር ሊጉን በ46 ነጥብ እየመራ ይገኛል።
መቻል በ41 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ39 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሻሸመኔ ከተማ በ13 ሀምበሪቾ ዱራሜ በ8 ነጥብ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሃዋሳ ከተማ አጥቂ አሊ ሱሌማን በ12 ግቦች ሲመራ የባህር ዳር ከነማው ቸርነት ጉግሳ በ11 ጎሎች ይከተላል።
የድሬዳዋ ከተማው ቻርልስ ሙሲጌ፣ ምንይሉ ወንድሙ ከመቻል፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኤርቦ እና የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ታረቀኝ በተመሳሳይ 9 ግቦች ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።