ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች - አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሃገራት ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዙሪያ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

አቶ አሕመድ በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ በተደረገ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መድረክ ላይ በነበራቸው ተሳትፎ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እያደገ የመጣውን ፈተና ለመቋቋም የደቡብ ደቡብ ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሃገራት በማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም አስረድተዋል።

እኛ ለቀጣናው ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስርና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረግን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በአረቡ ዓለም ግንኙተን ላይም ጉልህ ሚና እንዳላት ገልጸዋል።

ዓለም እየገጠሟት ያሉትን የተለያዩ ፈተናዎች ለመቋቋምም የደቡብ ደቡብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከዓባል ሃገራት ጋር ያላትን ኤኮኖሚያዊ ትስስር እንደሚያጠናክርላትም ነው አቶ አሕመድ ሽዴ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የአፍሪከ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማዕከል መሆኗን በውይይቱ ላይ ያነሱት አቶ አሕመድ ይህም በቀጣናው እና በአህጉሩ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

የብሪክስ አባል ሃገራት በኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት በቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ ረገድ በትብብር መስራት የሚችሉበት ሁኔታም ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም