የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ለትንሳኤ በዓል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ለትንሳኤ በዓል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ለትንሳኤ በዓል የሚውሉ ምርቶችን ለሸማቾች ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በመንግስት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱና ቀዳሚው ነው።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሌማት ቱሩፋት፣ የከተማ ግብርና፣ የመስኖ ስንዴና ሌሎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ሥር የተቋቋመው የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት እየሰሩ ካሉ ተቋማት መካከል ይጠቀሳል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቅ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ አርሶአደሮችን ለማቋቋም፣ ለስራ እድል ፈጠራና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የተቋቋመ ነው።
ማዕከሉ እንቁላልና ወተት በማምረት ከራሱ ሱቆች በተጨማሪ በከተማዋ ባሉ ዩኒየኖች አማካኝነት እንዲሁም ከመንግስት ተቋማት ጋር በተደረሰ ስምምነት ምርቶቹን ለሸማቾች እያቀረበ ይገኛል።
በዚህም ማዕከሉ ለትንሳኤ በዓል በርካታ ዶሮና እንቁላሎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከተቋቋመበት 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በዶሮ ፣ እንስሳት ማድለብና ወተት ላም እርባታ በ104 ማህበር የተደራጁ 500 በላይ ሰዎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉንም አስረድተዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ጨምረው አንደገለጹት አሁን ላይ በማዕከሉ በቀን ከ28 ሺህ በላይ እንቁላልና እስከ 900 ሊትር የሚጠጋ ወተት ይመረታል።
ተቋሙ የልህቀት ማዕከል በመሆን በዘርፉ ምርምር ለማከናወን ራሱን በሰው ኃይል እያደራጀ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።