ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ይደገፋል - የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት 

ጋምቤላ፤ሚያዝያ 23/2016  (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረዉን ጥረት እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት ገለጸ። 

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት አተገባበር ዙሪያ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል ። 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የጤና አገልግሎት ሽፋን ከፍ ለማድረግ በገባችው ቃል ኪዳን መሠረት በጤናው ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። 

የጤና አገልግሎቱን ሳይቆራረጥና ፍትኃዊ በሆነ መልኩ ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን  ገልፀዋል። 


 

በተለይም መደበኛና መደበኛ  ባልሆኑ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን በማቀፍ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል። 

ህዝቡን በዝቅተኛ ወጪ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን በማከል። 

በተለይም በመድኃኒት አቅርቦቱ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ፕሮግራሙ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። 

ዜጎች በገንዘብ እጦት ምክንያት የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይቀሩ ጥረቶች  መኖራቸውን ገልፀው፤ በጋምቤላ ክልልም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮት ጋትዊች በበኩላቸው መንግስት ህብረተሰቡን ካልተጠበቀ የጤና ወጪ ጫና ለመታደግና ፍትኃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን  አብራርተዋል። 

በዚህም ባለፉት ዓመታት የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ባሉ 11 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። 

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳለጥና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በተለይም ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን በማህበረሰብ የጤና መድን አገልግሎት አማካይነት  ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም