ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 23 /2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም  መሆኑን   ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በኢፌዴሪ አየር ኃይል ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱም ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አየር ኃይል በላቀ የስራ ትጋትና ጥራት እንደ ሀገር ያለንን ሀብት ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አንዱ ማሳያ የሆነ ተቋም ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከተጣለበት ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር በግብርናው ልማት በኩል ቀድሞ አላግባብ ጥቅም አልባ ተደርጎ የነበረውን የተቋሙን መሬት ወደ ልማት በመቀየር ያስመዘገበው ታላቅ ስኬት በሀገር ደረጃም አርዓያነት ያለው አኩሪ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰላም ወጥቶ ለመግባትም ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ለተያዘው የልማት ጉዞ የሀገር መከላከያ ያፀናው ሰላም ወሳኝ መሆኑን ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገር ባለው ክብርና ዝና አንቱታን ያተረፈ ትልቅ ተቋም መሆኑን አውስተው የግዛት አንድነታችን እንዲሁም ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ ለሀገራችን መድህን የሆነ አንጋፋው የአቭዬሽን ተቋም መሆኑንም ጠቁመዋል።

ቢሾፍቱ በሚገኘው የአየር ኃይል መምሪያ ግቢ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት አስተዳደሩ ለጀመረው የሌማት ትሩፋትም ጭምር በአርዓያነት የሚወስዱት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጃንጥራር አባይ ለዚ ሁሉ የተቋሙ ሰኬት አሻራቸውን ላኖሩ አመራሮችና አባላት ምስጋናቸውን አቅረበዋል።


 

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደገለጹት በሀገሪቱ የተጀመረው ተቋማትን ውብ እና ፅዱ አድርጎ የመገንባቱ ተግባር በአየር ኃይል ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ካቢኔያቸው በተቋሙ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሞራል ስንቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተቋማዊ ሪፎርሙ ወዲህ የአዲስ አበባ አስተዳደር በርካታ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ ለተደረገላቸው ድጋፍ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ልዩ አድናቆት እና ክብር እንዳላቸውም ገልፀዋል።

በዕለቱ የግብርናውን ልማት እና ሌሎች ከለውጡ ወዲህ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ከንቲባ አዳነች አቤቤና ካቢኔያቸው ተዘዋውረው መመልከታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም