ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2016(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ መጪውን  የትንሳኤን በዓል ሲያከብር ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል።

በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል  የትንሳኤ በዓል አንዱ ነው።

ህዝበ ክርስቲያኑም በአሉን በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስነ ስርአቶች፤ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በማዘጋጀት በደመቀ ሁኔታ እንደሚያከብሩት ይታወቃል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት  ለበአሉ ከሚደረጉ ዝግጅቶች ጋር በተያያዘ  የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ  ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ።

ኮሚሽኑ የመጪው የትንሳኤ በዓል አስመልክቶ  የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ማድረጉን ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የህዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ስለ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አጋላጭ ምክንያቶችና መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አድርጎ ከአቅም በላይ በሆነ መንስኤዎች ለሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በግብአትና በሰው  ኃይል  ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ  ማድረጉን ነው የገለፁት ።

ለስራ ፍጥነት ሲባል በአንድ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀም ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

በምግብ ማብሰልና ሌሎችም አገልግሎቶች ወቅት ከአካባቢው ተቀጣጣይ ነገሮችን ማራቅና ሻማና ሌሎችንም ነገሮች ለኩሶ መሄድም የአደጋ መንስኤ ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

ህብረተሰቡ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በነፃ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111555300 በመደወል ለኮሚሽኑ ማሳወቅ እንደሚችሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም