ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽሀፈት ቤት ሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 22/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት ሕንጻ ግንባታ ለማከናወን  በጅግጅጋ  ከተማ ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የጽህፈት ቤቱን ህንጻ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ መስጠፌ ሙሐመድ ናቸው። 

ለቅርንጫፍ ጽህፈቱ  ቤቱ ህንጻ ግንባታ ከ300 ሚሊዮን ብር ወጪ መመደቡ በዚሁ ወቅት ተገልጿል። 

የጽህፈት ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ተቋሙ ለክልሉ ጤና ተቋማት የሚያቀርበውን መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በቅርበት ለማድረስ እንደሚያስችለው ተጠቅሷል። 

አገልግሎቱ ለቢሮ ኪራይ እና ለመጋዘን አገልግሎት የሚያወጣውን ወጪም እንደሚያስቀርለት ተመልክቷል። 

በተያያዘም በሚኒስትሯ የተመራው ልኡክ በሶማሌ ክልል በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ በግንባታ ላይ ያለውን ክልላዊ የበሽታዎች መቆጣጠርና መከታተያ ማዕከል ጎብኝቷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የምህንድስና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ሱቢር ኢብራሂም፣ የማዕከሉ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ተናግረዋል። 

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ በክልሉ የሚከሰቱ በሽታዎች ለመለየት ወደ ሌላ አካባቢ ይላክ የነበረው የናሙና ምርመራ እንደሚያስቀር ጠቅሰዋል። 

በተመሳሳይ በ180 ሚሊዮን ብር ወጪ በጅግጅጋ፣ በጎዴና በዶሎ አዶ ከተሞች ለድንበር ዘለልና ለአስቸኳይ የጤና አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ የምርመራ ማዕከላት እየተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የጤና ሚኒስትሯ የጅግጅጋ ዩኒሸርሲቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍልና የታካሚዎች ካርድ ክፍል የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም