ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥና ብቁ አመራር ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ሚና ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥና ብቁ አመራር ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ሚና ተጠናክሮ መቀጠሉን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

በአካዳሚው በሁለት ወራት ብቻ ከ120 በላይ የአፍሪካ አገራት አመራሮች ሥልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፤ አካዳሚው ከኢትዮጵያም ባለፈ በመላ አፍሪካ ብቁ መሪዎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥና ብቁ አመራር ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ሚና ከጥንት እስካሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቀድሞውን የኬንያ መሪ ጆሞ ኬንያታ እና የነፃነት ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላ ማሰልጠኗን አስታውሰው፤ በዘመናዊ የአመራር ማሰልጠኛ በርካቶች እየሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አካዳሚው የአፍሪካን ችግር የሚፈታ ብቁ አመራር ለማፍራት በሚያስችል መልኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ሥልጠና ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ገልጸው፤ ይህንን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አካዳሚው በአህጉሪቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ተናግረው፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ120 በላይ የአፍሪካ አገራት አመራሮች ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በተሟላና ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተገነባው አካዳሚው ዓላማውም የሚደነቅ በመሆኑ የሁላችንም ድጋፍና እገዛ ያስፈልገዋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የላቀ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን በማቅረብ ሌሎች አገራትም ይህንን መልካም አርዓያ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም