ቀጥታ፡

አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተቀናጀ መንገድ የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ድሬደዋ ፤ ሚያዝያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተቀናጀ መንገድ የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሀመድ ገለጹ።

"ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ አስተዳደር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሐሰን መሀመድ በዚሁ ወቅት፤ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ አላማ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፣ ገቢ ምርትን መተካት፣ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማፋጠን መሆኑን አስታውሰዋል።

በ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በመላው ሀገሪቱ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪው በተደረጉ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስና የሙያ ድጋፎች የተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ስራ ተመልሰው ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስችለዋል ብለዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ ጭምር አበረታች ጅምር ውጤቶች መመዝገባቸውን አቶ ሐሰን አስረድተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ጉዳይ አሁንም በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተቀናጀ መንገድ የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት አመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአስተዳደሩ ሰባት የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በንቅናቄው በሚደረገው ድጋፍ የተበረታቱ አዳዲስ የውጭና የአገር ውስጥ የኢንቨስተሮች በብዛትና በጥራት ወደ ስራ እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህን አበረታች ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስራዎች እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የድሬዳዋ አምራች ኢንዱስትሪ የአስር አመት ፎኖተ ካርታ እና የምስራቅ ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ ላይ የፌደራል የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች እና የምስራቅ የአገሪቱ ክልሎች የኢንዱስትሪ ተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም