በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶች እየለሙና ተግባራዊ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶች እየለሙና ተግባራዊ እየተደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2016(ኢዜአ)፡-የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶች እየለሙና ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሚሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የግብርና ምርት ግብዓት አቅርቦት አሰራርን (E-Voucher) በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲጂታላይዝድ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሚሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፍሬው ተገኝ፤ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶች እየለሙና ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተባበሩት መንግስታት የካፒታል ዴቨሎፕመንት ፈንድ ጋር በመተባበር የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓት የአቅርቦት አሰራርን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለአብነትም ባለፉት አመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና ሲዳማ ክልሎች የግብርና ምርት ግብዓት አቅርቦት አሰራር የሙከራ ትግበራ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የሙከራ ትግበራው በአራት ቋንቋ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሳወቅ፣ ለክፍያ፣ ኢንሹራንስና ግብዓቶች የሚገኙባቸውን ማዕከላት ለማወቅ እየተገለገሉበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ አመታትም ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር ሀገር አቀፍ የግብርና ምርት ግብዓት አቅርቦት አሰራር አገልግሎትን ለማስፋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ አርሶ አደሩ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በአጭር ሂደት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በተባበሩት መንግስትት ካፒታል ዴቨሎፕመንት ፈንድ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም ማማ፣ አሰራሩ አርሶ አደሮች በአጭር ሂደት ቀልጣፋ አገልግሎት ባሉበት ቦታ ሆነው ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሶስት አመታት የግብዓት አቅርቦትን በግብርና ምርት ግብዓት አቅርቦት አሰራር መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ከግብርና ትራንስፎርሚሽን ኢንስቲትዩት ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።