የግል ባለሃብቶች የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ስቴሽን ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

የግል ባለሃብቶች የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ስቴሽን ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2016(ኢዜአ)፡- የግል ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ባለፈ የቻርጅ ስቴሽን ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ  የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ምትኩ አስማረ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማዋ በቀን ውስጥ ከሚደረገው 3 ነጥብ 4 ሚሊየን የትራንስፖርት ምልልስ ውስጥ 31 በመቶው በብዙኃን ትራንስፖርት የሚሸፈን ነው።

የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን መጠቀም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንደ አገር እየተከናወነ ያለውን ሥራ ለመደገፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው።


 

በተለይም ኢትዮጵያ ነዳጅ ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲቀር በማድረግ ለኢኮኖሚው አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።

መንግሥትም ለብዙኃን ትራንስፖርት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ በኤሌክትሪክ  የሚሰሩ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው ያለው የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ስቴሽን  በቂ ስላልሆነ ባለሃብቱ በዚህ ላይ ቢሳተፍ እራሱንና አገሩን ይጠቅማል ብለዋል።

ቢሮው በዘርፉ ለተሰማራው የግል ትራንስፖርት ሰጪ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የግል ባለሃብቶች በኤሌክትሪክ ቻርጅ ስቴሽኖች ላይ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።


 

መንግሥት 100 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የከተማ አውቶቡሶች ግዥ በመፈፀም በአጭር ጊዜ ለማስገባት ሥራ መጀመሩንም ነው የገለፁት።

በተጨማሪም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የከተማ አውቶቡሶችን በቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ሕብረተሰቡ አውቶቡሶች በስንት ሰዓት እንደሚደርሱ መረጃ የሚያገኙበት የመረጃ ሥርዓት በመርካቶ ተርሚናል ሥራ መጀመሩንና በሌሎች ለማስፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እየገጣጠመ እንደሚገኝና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የመጀመሪያዎቹ 216 ተሽከርካሪዎች መገጣጠማቸውን የገለፁት ደግሞ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሰጠኝ እንግዳው ናቸው።


 

በቬሎሲቲ ኤክስፕረስ ድርጅት አማካኝነት 20 የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችና ሁለት ኤሌክትሪክ ከተማ አውቶቡሶች በሙከራ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።       

አውቶቡሶቹ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ከመሆናቸው ባሻገር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሆነው መዘጋጀታቸውንም ነው የገለፁት። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም