ለትንሳኤ በዓል ሕገ-ወጥ ግብይት እንዳይኖር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለትንሳኤ በዓል ሕገ-ወጥ ግብይት እንዳይኖር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2016(ኢዜአ)፦ ለትንሳኤ በዓል ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎችንና ማጭበርበሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
ለበዓሉ የኑሮ ውድነትና ገበያ ማረጋጋት ላይ የሚሰራ የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከፖሊስ፣ ከሰላምና ደኅንነት፣ ከደንብ ማስከበርና ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተውጣጣና እስከ ወረዳ የተደራጀ ነው ተብሏል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከበዓሉ ዋዜማ እስከ ፍፃሜ የተጠናከረና የተቀናጀ የፀጥታ ስምሪት መስጠት በሚያስችለው የጋራ ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።
በዚሁ ጊዜ ለትንሳኤ በዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ላይ አላስፈላጊ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ግብረ- ኃይሉ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል ተብሏል።
የገበያ ማዕከላት ሰላማዊና የተረጋጉ ማድረግ፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ ቤተ-እምነቶች ሲሄዱና ሲመለሱ ሰላምና ፀጥታውን አስተማማኝ ማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቋል።
የምግብ ፍጆታ ምርቶች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳይከማቹ በመጋዘኖች ላይ ፍተሻና ክትትል የሚያደርግ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
በአምስቱም የመግቢያና መውጫ በሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዳይኖር መከላከል የግብረ-ኃይሉ ዋነኛ ሥራ ይሆናልም ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ በበዓላት ጊዜ የሚያጋጥሙ ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎችና ማጭበርበሮችን በተቀናጀ መልኩ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
መጪው የትንሳኤ በዓል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸው፤ ዕቅዱ ወደ መሬት እንዲወርድ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የንግድ ሥርዓቱ ፍትሃዊና ሕጋዊ ሆኖ የከተማዋን ነዋሪ እርካታ የሚጨምር እንዲሆን የጋራ ግብረ-ኃይሉ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በምግብ ፍጆታዎች ላይ ባዕድ ነገር የሚጨምሩ ሕገ-ወጦች ላይም ሰፊ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
በዓሉን ምክንያት አድርጎ ሕገ-ወጥ ዕርድ እንዳይካሄድ ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
ወጥ የሆነ የሸቀጦች ዋጋ አለመኖር፣ የተዘበራረቀ የደረሰኝ አጠቃቀም፣ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ማነስ፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥራው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የግብረ-ኃይሉ አባላት አንስተዋል።
በገበያ ውስጥ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላትና ያለደረሰኝ የሚፈጸሙ ግብይቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገሩት።
የቁም እንስሳት ግብይት የሚካሄድባቸው ቦታዎች ላይ ሕገ-ወጥ ደላሎችን የመቆጣጠር ሥራም የግብረ-ኃይሉ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ እና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቅድስት ስጦታው ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ የተከማቹ ምርቶችን እንዲያጋልጡ ጠይቀዋል።
በግብይት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የማታለልና የማጭበርበር ተግባራትን በንቃት መከታተልና ሕብረተሰቡ ለግብይት ገንዘብ ይዞ ሲወጣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
ለበዓል አስፈላጊ ግብዓቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር የጋራ ግብረ-ኃይሉ በትኩረት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።
የትራፊክ መጨናነቅ በከተማዋ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር አፋጣኝ መፍትሄ መስጠትም የግብረ ሀይሉ ዋነኛ ስራ ይሆናል ተብሏል።