ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብተው የተጠናቀቁ ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ ማምረት ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብተው የተጠናቀቁ ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ ማምረት ገቡ
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 22/2016(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል።
በድሬዳዋ ዛሬ የተጀመረውን "የኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" የሶስተኛ ዙር ንቅናቄ ምክንያት በማድረግ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፋብሪካዎች ተመርቀው አገልግሎት ጀምረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እና የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ፋብሪካዎቹን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ተመርቀው ወደ አገልግሎት የተሸጋገሩት የከባድ መኪና ተሳቢ ማምረቻ፣ የባለ ሶስትና አራት እግር የመኪና መገጣጠሚያ፣ የህክምና ቁሳ ቁሶች ማምረቻ እና የታሸጉ ውሃ ፋብሪካዎች ናቸው።
ፋብሪካዎቹ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውም ተገልጿል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድሬዳዋን የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ሂደት ጥሩ መንገድ ላይ ይገኛል።
አስተዳደሩ ለባለሀብቶች የሚያደርገውን የተለያዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎችንም አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለባለሃብቶች የተደረገውን ድጋፍ ተከትሎ በኢንቨስትመንት ዘርፍ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አክለዋል።
በድሬዳዋ ዛሬ የተጀመረውን ሶስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምክንያት በማድረግ ዛሬ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪን እንቅስቃሴዎች የሚያጠናክር የፓናል ውይይት ይካሄዳል።