ለመጪው የትንሳኤ በዓል ጥራቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥጋና የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለመጪው የትንሳኤ በዓል ጥራቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥጋና የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- ለመጪው የትንሳኤ በዓል ጥራቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥጋና የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር እና የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የትንሳኤ በዓል ዝግጅት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰኢድ እንድሪስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ለመጪው የትንሳኤ በዓል ከ8 ሺህ 500 በላይ በሬዎች፣ በግና ፍየሎች ለእርድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው እንዳሉት በዓሉን ምክንያት በማድረግም የከብት ሥጋ በኪሎ 570 ብር፣ የፍየል ሥጋ 510 ብር፣ የበግ ሥጋ በኪሎ በ500 ብር እንደሚሸጥም ገልፀዋል።፡
ለበዓሉ በቂ እርድን በማከናወን ለልኳንዳ ቤቶች ለማቅረብ 37 ተሽከርካሪዎችን ማዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
በድርጅቱ ያሉ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች በተጨማሪ ለበዓሉ የሰው ኃይል እጥረት እንዳይገጥም ለእርድ እና ሥርጭት 200 ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዲሁም ለተረፈ ምርት ዝግጅት 50 ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቅጥር መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለበዓሉ እርድ በሚያከናውንበት ጊዜ ለቆዳው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ እንዲያስወግድ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕገ-ወጥ እርዶቹ በወንዞች አካባቢ፣ በሆቴሎች ጀርባና በተለያዩ ቆሻሻ ቦታዎች ስለሚከናወን ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ከማጋለጥ በተጨማሪ ሥጋው ስለሚመረዝ የጤና ሥጋትነቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሕገ-ወጥ እርድን የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
ለዚህም ሕብረተሰቡ ሕገ-ወጥ እርድ በመከላከል የተመረመረና ጤንነቱ የተረጋገጠ ሥጋ እንዲመገብ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አየለ ሳህሌ በበኩላቸው፤ በልኳንዳ ቤቶች ለበዓሉ በቂ ሥጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ከቄራዎች ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን እየሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ ሕገ-ወጥ እርድን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የሥጋ ምርመራ አገልግሎት ቡድን መሪ ከበበ ኤርቤቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሚቀርበው ሥጋ ጤናማነትና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ኮሚሽኑ የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎችን በመመደብ ከዋዜማው ጀምሮ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አብራርተዋል።