ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶች በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶች በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የበኩላችንን እንወጣለን

ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- ከየቤቱ የሚወጣውን ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶች በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የበኩላቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተጀመረው ንቅናቄ በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮችና በተለያዩ የዞን መዋቅሮችም እየተካሄደ ነው።
በሀዋሳ ከተማም ንቅናቄው የተጀመረ ሲሆን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት ከየቤቱ የሚወጣውን ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶች በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የድርሻቸውን ይወጣሉ።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የመሃል ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ዲላ አሻንጎ የአካባቢ ብክለት ጤናን ከማወክ ጀምሮ የከተማ ገጽታ ስለሚያበላሽ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ሃላፊነት መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
ለዚህም ከየቤት የሚወጣው ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶችን በአግባቡ ከማስወገድ በተጨማሪ ለይቶ በማስቀመጥ የጽዳት ስራ ማገዝ ይገባናል ብለዋል።
ለዚህም ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ለአካባቢ ብክለት የሚያጋልጡ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ጭምር ለአካባቢያቸው ንጽህና እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የኩል ፕላስቲክ ሪሳይክሊንግ ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ቶማስ በበኩላቸው ከስድስት ዓመት በፊት ተደራጅተው የጀመሩት ስራ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው ።
በተለይም ከኢንዱስትሪዎች፣ ከተቋማትና ከየቤቱ የሚወገዱ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ ባሻገር የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራንም እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከተማዋን ከብክለት ለመከላከል የሚሰራውን ስራ በማገዝ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን እንዲያዘመን የተጀመረው የንቅናቄ ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።
ሀዋሳ ከተማን ጽዱ፣ውብና ምቹ ለማድረግ የሚከናወነው የጽዳት ስራ ውጤታማ እንዲሆን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን ማስተካከል ይገባል ያለው ደግሞ የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማው ወጣት እስራኤል ሸከካ ነው።
በሚኖርበት ክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ስራ እንደሚሰሩ ገልጾ ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።
ማህበረሰቡ ከቤቱ ከሚያወጣው ቆሻሻ ጀምሮ የፕላስቲክ አጠቃቀሙን ቢያስተካክል ችግሩን መቀነስ እንደሚቻልም ተናግሯል።
የጤና ባለሙያዋ ሲስተር ሲሳይ ፈለቀ በበኩሏ የአካባቢ ብክለት በአየር ንብረት ለውጡ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየተበራከተ መምጣቱን ገልጸዋል።
ችግሩ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚጠይቅ ቢሆንም ለመፍትሔው የእያንዳንዱ ግለሰብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የፕላስቲክ አወጋገዳችንን በማስተካከል ጤናችንን መጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት።
የተጀመረው የንቅናቄ መድረክም የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ውስጥ የሚተገበረውን የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የሚያግዝና ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል በመሪ ሐሳብ ለቀጣይ ስድስት ወራት በተቀናጀ መንገድ የሚተገበር ንቅናቄ መጀመሩ ይታወሳል።