የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ይገባል- ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ይገባል- ዶክተር መቅደስ ዳባ
ጅግጅጋ ፤ ሚያዝያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስቀድሞ በማቀድ እና በጀት በማዘጋጀት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ጠንካራ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሰብ ከፍተኛ የአመራር አካላት የተሳተፉበት የህብረተሰብ ጤና የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በጅግጅጋ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰቱ አጣዳፊ የጤና አደጋዎች እየተበራከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ኮቪድ 19፣ የውሃና የኮሌራ እንዲሁም የኩፍኝ ተላላፊ በሽታዎችን አንስተዋል።
በሀገራችን እየተከሰቱ እና ሊከሰቱ የሚችሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የባለ ድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ይገባል ብለዋል።
የ ‘ጽዱ ኢትዮጵያ’ ዲጂታል ቴሌቶን ዘመቻ ለጤና ዘርፉ መሻሻል እና ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ሁሉም ዜጋ ዘመቻውን እንዲቀላቀል ጥሪ አቀርበዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው "የሀገራችን የጤና ስርዓት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ የተነሳም የሚከሰቱ የጤና አደጋዎችን ለመቁጣጠር እየተቻለ ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስቀድሞ በማቀድ እና በጀት በማዘጋጀት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ፤ ኢንስቲትዩቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በበርካታ ወረዳዎች የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት በአብዛኛው መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
የወባ በሽታንም ወረርሽኝ ደረጃ ሳይደርስ ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ከ19 ሚልዮን ብር በላይ በጀት ለዚሁ ታስቦ መከፋፈሉን ጠቅሰዋል።
ኮሌራ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠርም 10 ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ክትባት ተሰጥቷል ብለዋል።
የኩፉኝ በሽታንም በክትባት ለመከላከል ለ14 ሚልዮን ህፃናት ክትባት መሰጠቱን አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የፌዴራል የጤና ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጤና ቢሮ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።