የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢትዮ-ተርክዬን ንግድና ኢንቨስትመንት የሚያጠናክር ነው - አምባሳደር በርክ ባራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢትዮ-ተርክዬን ንግድና ኢንቨስትመንት የሚያጠናክር ነው - አምባሳደር በርክ ባራን
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢትዮ-ተርክዬን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን ገለጹ።
ከአፍሪካ አገራት ጋር የሚኖራትን የልማት ትብብር ለማጠናከር ተርክዬ በትኩረት እየሰራች መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የተርክዬ የልማት ትብብር መሰረቶች የህዝቦችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
የአፍሪካን አጀንዳ 2063 እቅዶች ታሳቢ በማድረግም በአህጉሪቷ የህዝቦችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በነፃ የትምህርትና ሥልጠና ዕድሎች ተርክዬ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ተርክዬ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ትብብር ባሻገር የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በትምህርትና ስልጠና ሁለቱ አገራት ይበልጥ ተቀራርበው የሚሰሩ መሆኑን አምባሳደር በርክ ባራን አረጋግጠዋል።
በኢትዮ-ተርክዬ መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርም 700 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የማሻሻያ የሁለቱን አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ገንቢ ሚና ይጫወታል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና ተርክዬ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1896 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።