ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማልማት የጀመራቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2016(ኢዜአ)፦ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማልማትና ቴክኖሎጂ ተኮር ሥራዎችን ለማስፋት የጀመራቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ሲል የፌዴራል  ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን  አባላት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ አድርጓል። 


 

በሚኒስቴሩ ሥር የሚገኙ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግርና በፈጠራ ላይ እያከናወነ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የቡድኑ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ብቁ እና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እያደረገ ያለው ሥራ የበለጠ ሊጠናከር ይገባልም ብለዋል።

በዚህም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ ልማት፣ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ሀገር ሥራ ገበያ ስምሪት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በሌሎች ዘርፎች እያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

አዳዲስ ዕይታዎችና ቴክኖሎጂ ተኮር ሥራዎች እንዲሁም እራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ የተከናወኑ ተግባራት በጥሩ ጅምር  ላይ መሆናቸውን ቡድኑ መመልከቱን ተናግረዋል።

የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለመቆጣጠር፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና ሥራውን ለመምራት የተከናወነ ተግባር ትልቅ እምርታ የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ክህሎት መር እና አምራች የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች እንዲሁም አምራች የሆኑ ማሽነሪዎችን የመፍጠር ሥራዎች የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራም የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

መልካም ተሞክሮዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሰፉ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

ቡድኑ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሃኑ አለቃ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በተሰሩት ሥራዎች መሻሻሎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በዚህም የሥራ ገበያን ዲጂታል በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ዳታቤዝ ማዕከል ተገንብቶ ሥራ እና ሠራተኛን የተመለከቱ መረጃዎችን በአንድ የማስተዳደር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገሪቱ እና በውጭ የሥራ ገበያን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና ሕገ-ወጦችን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም