ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ድጋፍ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ የኮሪያ ዓለም አቀፍ  የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ሃንዳክ ጆ ገለጹ። 

በኢትዮጵያ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በመደገፍና በማበረታታት ስታርት አፖች በስፋት እየተዋወቁ ይገኛሉ።

በዘርፉ የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዲኖር ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኮሪያ ዓለም አቀፍ  የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሃንዳክ ጆ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ  አሁን ላይ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ትግበራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በተለይም በቅርብ አመታት በስታርት አፖች ለተሻለ የፈጠራ ስራ ምቹ ምህዳር መኖሩን አድንቀዋል።

ኮይካ የ10 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በመያዝ ለስታርት አፖች የተቋማት ኢንኪዩቤሽን ማዕከላት ግንባታ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚደረጉ ጥረቶችን በማገዝ ረገድ የኮይካ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስታር አፖች እንዲሁም በአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ ዘርፍ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ጥረቶች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት 50 ብቻ የነበሩት ስታርት አፖች አሁን ላይ ከ900 በላይ ጀማሪ፣ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ እና ወደ ገበያ የገቡ ስታርት አፖች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቶ በነበረው አውደ ርዕይ 300 የሚደርሱ ስታርት አፖች ለእይታ ቀርበው የተሻሉ የስራ ሃሳብ የነበራቸው  ስታርት አፖች መሸለማቸው ይታወሳል።

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም