የሚዲያ ተቋማቱ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ሚናቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተጠቆመ

ሐረር ፤ ሚያዚያ 22/2016 (ኢዜአ)፡- የሚዲያ ተቋማት የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን እየሰሯቸው ያሉትን ስራዎች ማጎልበት እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሐረር ቅርንጫፍን እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተው ከተወካዮቻቸው ጋር ውይይት አካሂደዋል።
 

የቋሚ ኮሚቴው አባልና የሚዲያ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አቦኔ ዓለም እንዳመለከቱት፤ የምልከታው ዋና ዓላማ የተቋማቱን ቅርንጫፎች የሥራ አፈጻጸምና ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲሁም እያጋጠማቸው ያለውን ተግዳሮት ለመለየትና ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ ነው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሐረር ቅርንጫፍዎች በተወሰነ የሰው ሃይል ሰፊ አካባቢዎችን ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑንና የተሻለ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም በተግባር መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሐረር ቅርንጫፍ ከምርጫ ማግስት ጀምሮ አዲስ አደረጃጀት በመዘርጋት ለዜጎች በምርጫና በሌሎች ግንዛቤን ከመፍጠር እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እያከናወኑ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን በማውሳት።

የሚዲያ ተቋማቱ በተለይም ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ግንዛቤን ከማጎልበት አንጻር የተሻለ ስራ ማከናወን ይገባቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ከመታገል አንጻርም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶቹ እያከናወኑ የሚገኘውን ስራ ማጎልበት ይገባቸዋል ያሉት ወይዘሮ አቦኔ፤ በተለይም መድረኮችን ብቻ ተከትሎ መዘገብ ሳይሆን አቅደው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴ አባል እጅጉ መላኬ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት በህዝቦች መካከል በተለይም በሐረር አካባቢ ያለው መልካም እሴት እንዲጎለብትና የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮች እንዲቀረፉ የሚሰሯቸው ስራዎች አበረታች ነው ብለዋል።


 

የሚዲያ ተቋማቱ የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበው በተለይም በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ እየታዩ የሚገኙ ተግዳሮቶችም የሚፈቱበት መንገድ መመቻቸት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ካቀደው 85 በመቶ ስራ ማከናወኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮዽያ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ቦጋለ ናቸው።


 

በተለይም የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ያቀረቡትን ለትምህርት ቤቶች እና ለሁሉም ማህበረሰብ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ምክረ ሀሳብ እንደ ግብዓት በመውሰድ በቀጣይ የተሻለና ተከታታይነት ያለው ሥራ ይሰራል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ድረስ በአካል ተገኝተው ያደረጉት ጉብኝት ለተቋሙ ትልቅ ግብዓት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በኢትዮዽያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የሐረር ስቱዲዩ አስተባባሪ አቶ አብዱሰላም መሐመድ ናቸው።


 

በተለይም ተቋሙ ያለውን ውስን የሰው ሃይል በመጠቀም እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ገንቢ ግብረ መልስ በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም