ቀጥታ፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጣሊያን የካራቢኔሪ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ ተቀብለው አነጋገሩ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጣሊያን የካራቢኔሪ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ ተቀብለው አነጋገሩ።

በኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑክ እ.ኤ.አ ጁላይ 2022 ወደ ጣሊያን ሮም ተጉዞ ከጣሊያን ፖሊስ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ በተደረሰ ስምምነት መሠረት የጣሊያን የካራቢኔሪ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን ጎብኝተዋል፡፡

ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው ከዚህ ቀደም በሮም ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች አፈፃፀም እና ተጠናክረው በሚቀጥሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
 
በውይይታቸው ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጥበቃን የሚያግዙ የፖሊስ ፓትሮል ጀልባዎችን በድጋፍ ለመስጠትና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ፣ በፖሊስ አመራር፣ በፎረንሲክ ሳይንስ እና በቪ አይ ፒ ጥበቃ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም ለመገንባት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ እየተገነባ ላለው የፎረንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩትን በማቴሪያል ለማደራጀት ቃል ገብተዋል፡፡ 

በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋት የሆኑ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተቀናጀና በትብብር ለመከላከል መስማማታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም