ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍ ምርታቸውን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ባለሀብቶች ገለጹ

ደሴ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡-   በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን እንደጨመረ በደሴ ከተማ የሚገኙ ባለሃብቶች ገለፁ።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በችግር ውስጥ የቆዩ 255 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ተግባር መግባታቸው ተጠቁሟል።

''ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት'' የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሄዷል።

በከተማው የቢግ ሳሙና እና ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ድልባንተ መካሽ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በተደረገላቸው ድጋፍ የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት ችለዋል።

በዚህም በቀን ከ1 ሺህ 500 ካርቶን በላይ የተለያየ ሳሙና በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን አመልክተው፤ የአካባቢውን ገበያ ከማረጋጋት ባለፈ ከውጭ የሚመጡ ሳሙናዎችን መተካት መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቀን አንድ ሺህ ሲሊንደር ኦክስጂን በማምረት በዘርፉ የሚስተዋለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታት መቻሉን ጠቁመው፤ ከምርት ሽያጭም የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የበለጠ እንዲሰሩ ከማነሳሳቱ ባሻገር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚያቀርቧቸውን ችግሮች በመፍታት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።

አቶ ድልባንተ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መንግስት ቀደም ሲል በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት እጥረት፣ የውሃ፣ የመንገድና ሌሎችንም መሰረተ ልማቶች ተግዳሮቶች በማስተካከል ወደ ተሟላ ስራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።    

በተለይ አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ምርታማ እንዲሆኑ ማደረጉን ጠቁመው፤ ተጠቃሚነታቸው ከማረጋገጥ ባሻገር ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

ሌላዋ የፀሐይነሽ የወተት ላም እርባታ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት ወይዘሮ ፀሐይነሽ ግዛው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሰጠው ትኩረት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም በብዛትና ጥራት ተወዳዳሪ ምርቶችን በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን አመልክተው፤ "ገበያውን ለማረጋጋትና ዜጎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻለ ነው" ብለዋል።

በቀን ከ200 ሊትር በላይ ወተት፣ 30 ኪሎ ግራም አይብና ከ50 ኪሎ ግራም በላይ የቼዝ ምርት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ፀሐይነሽ እንደገለጹት፤ በንቅናቄው ለባለሃብቶች የመሸጫና የመስሪያ ቦታ ጭምር ተመቻችቶ ምርታማ እንዲሆኑና ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ አድርጓል፡፡

የዘርፉ ማነቆዎችም እየተፈቱና አስቸጋሪ አሰራሮች መፍትሄ እያገኙ መምጣት መቻላቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የደሴ ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ አለባቸው ሰይድ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪዎች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ አግዟል።

በዚህም በከተማው የሚገኙ 169 ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቱት ምርት ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

ኢንዱስሪዎች ከ29 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት ማምረት እንደቻሉ ጠቅሰው፤ በዘርፉም ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት በጥናት ጭምር በመለየት ለባለሀብቶች እየተላለፈ ነው።

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለሃብቶችን ጥያቄዎች በቅንጅት ምላሽ በመስጠት ምርታማነትን ለማሳደግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በችግር ውስጥ የቆዩ 255 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት በመግባታቸው ዘርፉ ተነቃቅቷል።

በተለይ ለ241 ኢንዱስትሪዎች በተደረገው ልዩ ድጋፍ 33 ሺህ ቶን ተኪ ምርት በማምረት 195 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን አመልክተዋል።

በመድረኩ የክልልና የከተማ አመራር አባላት፣ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ ጥሩ አፈፃፀም ላሳዩ ባለሀብቶች እውቅና ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም