ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የግብርና ምርት የውጪ ንግድን ሰርተፍኬት ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና የውጭ ንግድ ምርት የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት /ፊያቶ/  በኤሌክትሮኒክ  ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት  ተደረገ።

ስምምነቱ በወረቀት ሲሰጥ የነበረውን  የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት /ፊያቶ /  ወደ ኤሌክትሮኒክ / ኢ-ፊያቶ/ ለመቀየር የሚያስችል ነው።

የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር  ወንዳለ ሐብታሙ፣ በኢትዮጵያ ትሬድ ማርክ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር  እውነቱ ታዬ እና የብሪስክ ሶሉሽን ኩባንያ ተወካይ ፒተር ኪርዋ ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርት የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማዘመንን  ታሳቢ ያደረገ ነው።

ባለሥልጣኑ “ኢ-ፋይቶ” የተባለውን የግብርና ምርቶች የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሥርዓት ዝርጋታን እውን ለማድረግ  ትሬድ ማርክ አፍሪካ ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢ- ፊያቶ የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት  ሥርዓት ግንባታን  ብሪስክ ሶሉሽን ኩባንያ  በአጭር ጊዜ ያከናውነዋል ብለዋል፡፡

ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅትም  የሀገሪቱን  የኤክስፖርት ምርቶች ግብይት ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ትሬድ ማርክ አፍሪካ  ዋና ዳይሬክተር እውነቱ ታዬ በበኩላቸው፤ የግብርና ምርት የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት  የአሰጣጥ ሥርዓትን ከወረቀት  ወደ ዲጂታል በስድስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምርቶችን የምትልክባቸው ሀገራት  የኢ-ፊያቶ ሰርተፊኬት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤  ወደ እዚህ ሥርዓት መገባቱ ለውጭ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ኢ-ፊያቶ ሰርተፊኬት ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ57 በላይ ሃገራት ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ በአፍሪካ ደግሞ አሥር ሃገራት የኢ- ፊያቶ ሥርዓት እየተጠቀሙ እንደሚገኝ በስምምነቱ ላይ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም