ቀጥታ፡

ሠራተኞች ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- የመንግስት እና የግል ተቋማት ሠራተኞች ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጠየቀ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ኮንፌዴሬሽኑ ሰራተኛው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና ጥያቄዎቹም እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በኢትዮጵያ በሠራተኛው ዘንድ ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች በሒደት ምላሽ እያገኙ ቢሆንም አሁንም ያልተመለሱ እና ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል።

ለዚህም ኮንፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ለአገሪቱ በርካታ ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸው፤ በየትኛውም ተቋማትና ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባህል ማእከል በተለያዩ የፓናል ውይይቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ135ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ  ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም