ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 400 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምዝገባ ተካሂዷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 400 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምዝገባ ተካሂዷል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 400 የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ማካሄዱን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ በ2018 በጀት ዓመት የ11 ሺህ 500 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምዝገባ በማካሄድ መብቶች እንዲጠበቁ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ የአዕምሯዊ ንብረት የፓተንት፣ የመገልገያ ሞዴል፣ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ፣ የንግድ ምልክት እንዲሁም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ላይ እየሰራ ይገኛል።
ባለፈው በጀት ዓመት 3 ሺህ መብቶች የመጠበቅ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ለ4 ሺህ 500 መብቶች ለመጠበቅ መታቀዱን ተናግረዋል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የ3 ሺህ 400 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምዝገባ መካሄዱንም ተናግረዋል።
በቀጣይ አመታት መብቶች የማስጠበቅ አቅምን በማሳደግ በ2018 በጀት ዓመት ለ11 ሺህ 500 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለሥልጣኑ የፓተንት፣ የንግድ ምልክት እና የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ የሚመሩበት ሦስት አዋጆች አፈጻጸም ደካማ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኅብረተሰብ ግንዛቤ ማነስና ፈጠራን ለማበረታታት የሚወሰዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ውጤታማ ያለመሆን ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዋጆቹ ዘመኑን በሚመጥን አግባብ እየተሻሻሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ግብርናን መሠረት ያደረጉ የፈጠራና የባህል መብቶች የሚጠበቁበት ሕግ እየተረቀቀ መሆኑንም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ከ30 ሺህ በላይ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ተመዝግበው ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።