ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ጉባዔ (አይ ዲ ኤ) ላይ ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የአፍሪካ ቀንድ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰቱ የተለያዩ አደጋዎች ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው ኢትዮጵያ እነዚህን ስጋቶች ለመቀነስ ለአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ በመርሃ ግብሩም ደንን መልሶ ማልማት፣ የአረንጓዴ ልማትን ማጠናከር፣ የአካባቢ ልማት ጥበቃን ማጎልበት ላይ አተኩራ እየከወነች ነው ብለዋል።
ለኑሮ የሚመች አካባቢን መፍጠር የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን በመግለጽ ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
በተጨማሪም መንግስት ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን እንደምሳሌ አንስተዋል።
በዚህም በሀገሪቱ የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታትና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እውን ለማድረግ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝምና በሌሎች የልማት ዘርፎች የ10 ዓመት የልማት እቅዶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በትምህርት፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በሀይል አቅርቦት ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችንና ውጤቶችንም ለአብነት አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናው ለእርቅና ለምክክር ቅድሚያ በመስጠት መሰራት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡ ሲሆን የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ እርቅና ምክክር እውን እንዲሆን ያከናወናቸው ተግባራትን ጠቅሰዋል።