በግብርና ሚኒስቴር የሚተገበረው የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ሚኒስቴር የሚተገበረው የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- በግብርና ሚኒስቴር የሚተገበረው የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ሲቻል መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮግራም በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ በGlobal Climate Fund (GCF) የፋይናንስ ድጋፍ በአለም ባንክ አመቻችነት የተገኘ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ በጀት 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥም 107 ሚሊዮን ዶላሩ የረጅም ጊዜ ብድር ሆኖ 58 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ የልማት ድጋፍ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሮግራሙ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በ9 ክልሎችና በ47 ወረዳዎች ላይ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራሞችን በመተግበር ተጨማሪ 706 ሺህ 133 ሰዎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በመንግስት፣ በዓለም ባንክ፣ በበGlobal Climate Fund (GCF) እና በሌሎች የልማት አጋር አካላት ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ መሬትን፣ ደንና የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት መጠቀም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የግብርና ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ በዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ብሎም የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ የፕሮጀክት ታስክ ቡድን መሪ አቶ ሚሊዮን አለማየሁ በግብርናው ዘርፍ ላይ መልካም ተሞክሮዎች መታየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህንን ለማስቀጠል በአለም ባንክ በኩል የሚደረጉ ድጋፎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው መንግስት በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የአለም አቀፍ የልማት አጋር አካላትና ለጋሾች በሚሰጡት ድጋፍ በርካታ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
የዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ከእነዚህ መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው ፕሮግራሙ በሚካሄድባቸው ተፋሰሶች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂ አሰራሮችን በማስፋፋትና የአፈር ለምነትን በማሻሻል በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ተግባራት በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ሀይሉ ናቸው፡፡