ኮሚሽኑ የቆላማ አካባቢና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ያማከሉ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲስፋፉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የቆላማ አካባቢና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ያማከሉ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲስፋፉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ
አዳማ ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የቆላማ አካባቢና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ያማከሉ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲስፋፉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የቆላማ አካባቢና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ያማከለ አካታች የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራትን ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ መክሯል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት ለፋይናንስ አካታችነት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
የህብረት ስራ ማህበረት መዋቅራዊ ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በቆላማ አካባቢና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነት ማረጋገጥ አንዱ የሪፎርሙ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ስምንት ክልሎች ያሉ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች አካታች የፋይናንስ አሰራር ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንም በዚሁ ወቅት አስታውሰዋል።
በነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበራት እንዲያደራጁና ለማኑፋከቸሪንግ እንዲሁም ለእርሻ ማሽነሪዎች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ጨምር ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በኮሚሽኑ የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ በበኩላቸው ለመሰረታዊ ማህበራትና ዩኒየኖች የፋይናንስ አካታችነት አሰራርና መመሪያዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ2 ሺህ በላይ በሚሆኑ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበረት በተዘጋጁ አሰራርና መመሪያዎች መሰረት 14ሺህ ለሚሆኑ አባላት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል።