አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሳውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ መልሶ ግንባታ ስራ በይፋ አስጀምሯል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኋላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግና በከተማ ፕላን እንድትመራ ለማስቻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ በአምስት ኮሪደሮች ተከፋፍሎ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ የከተማዋ ልማት ለሁሉም ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሳውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ መልሶ ግንባታ ሙሉ ወጪ እንደሚሸፈን ጠቁመው ህንጻው አንድ ቤዝመንት ያለውና ባለ አራት ወለል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ሕንጻ በሁለቱ አካላት ስምምነት በኮሪደር ልማት ምክንያት መፍረሱን ገልጸው አሁን ላይ የአካባቢውን ልማት በሚመጥን መልኩ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ህንጻውን በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለቤተ-ክርስቲያኗ የሚያስረክብ ይሆናል ተብሏል።
ግንባታው በፍጥነት፣ በጥራት እና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ከተማዋን ለማስዋብ የሚደረጉ ለውጦች የሚያስደስቱ ናቸው ብለዋል።
በመልሶ ማልማት ምክንያት የፈረሰውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ወጪ መልሶ ገንብቶ ለማስረከብ መወሰኑን አድንቀዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው ልማቱ በሁሉም ዘንድ የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ ከመልሶ ማልማት ስራው ጎን መሆኗን ጠቁመው ለተደረገው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ቀደምት የነበረው ህንጻ እንዲነሳ እና በከተማ አስተዳደሩ ውጪ ዘመኑን የዋጀ ህንጻ እንዲገነባ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ገንብቶ እንደሚያስረክባቸውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት ግንባታው የተጀመረው ሕንጻ በተለምዶ የመሃሙድ ሙዚቃ ቤት ተብሎ ሲጠራ የነበረው የቤተክርስቲያኗ ይዞታ ነው።