ኢትዮጵያ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራች መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 21/2016 (ኢዜአ)፡- አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተጨማሪ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ ፡፡
ዩኔስኮ ቅርሶችን የሚመዘግበው አገራት እ.አ.አ በ1972 የሚዳሰሱ ቅርሶችን ለመጠበቅ፤ እ.አ.አ በ2003 ደግሞ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለመጠበቅ በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ የፈረሟቸውን ስምምነቶች መሰረት በማድረግ ነው።
ቅርሶች በገንዘብ የማይተመኑ ትልቅ የአገርና የትውልድ ሀብቶች በመሆናቸው ዩኔስኮ ሁልጊዜም ትኩረቱ ቅርሶች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ላይ ነው ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባዉ አያሌዉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በሀገሪቱ የሚገኙ ቅርሶችን የመመዝገብ፣ የመመርመር፣ የመጠበቅና የማስተዳደር ተግባር ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ በሚሰጠው የሙዚየም አገልግሎት የሀገርን ቅርስና ታሪክ ለትውልድና ለውጭ ሀገር ዜጎች በማስተማርና በማሳወቅ ሀገራዊ ተልዕኮውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከክልሎች ጋር በመተባበር በብሔራዊ ደረጃ 2 ሺ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
በቅርስነት ተመዝግበው ከቆይታ የተነሳ ለተበላሹና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰባት የስዕልና የኪነ ሕንጻ ሃብቶች ጥገና መደረጉን አክለዋል፡፡
ቅርሶቹ በአማራ ፤በኦሮሚያ ፤በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ሲሆን የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የቀድሞ መኖሪያ ቤትም ጥገና ከተደረገላቸው ቅርሶች እንደሚካተት ጠቅሰዋል ፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥንታዊና ታሪካዊ የመሀመድ ባንጃዉ ቤት እና ብሔራዊ ሙዚየም ጥገና በቅርብ እንደሚጀምሩ በመጠቆም ፡፡
የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር፣ የባሌ ተራሮች እና በሀረር ክልል በድምቀት የሚከበረዉ “ የሸዋል ኢድ ” ሀይማኖታዊ ሥርዓት በዘንድሮ በጀት ዓመት የተካተቱ ቅርሶች ናቸው ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፤ እአአ በ 2024 ሐምሌ ወር በህንድ በሚካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ ላይ የመልካ ቁንጡሬ መካነ ቅርስና፤ የባልጨ መልካአ ምድራዊ አቀማመጥን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።
እአአ 2025 የወላይታ ሕዝብ ዘመን መለወጫ “ ጊፋታ” እና “ ሄር ኢሴ” የተሰኘ የኢሳ ባህላዊና አፋዊ የህግ ስርዓትን በዓለም በማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አክለዋል፡፡
በቀጣይ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የቡና ሥርዓት፣ ፊደል ፣ ጤፍ እና እንሰትን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ መለየታቸወን አብራርተዋል ፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪከ በዩኔስኮ በማስመዝገብ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች ሲሆን እአአ በ 1972 የዓለም ስምምነት ከፀደቀ ከ 51 ዓመታት በኋላ ሃገራችን ኢትዮጵያ 11 የሚዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች።
አፍሪካ በ 50 ዓመታት ዉስጥ 101 ቅርሶችን ያስመዘገበች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 11ዱ ቅርሶች የኢትዮጵያ ናቸዉ።
በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባህልና የተፈጥሮ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ሃገር ነች።