ኤልሳልቫዶር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ልትከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኤልሳልቫዶር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ልትከፍት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 21/2016(ኢዜአ)፡- ኤልሳልቫዶር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ልትከፍት መሆኑ ተገለጸ።
በኤልሳልቫዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሌክሳንድራ ሂል ቲኖኮ የተመራ ልዑክ ቡድን ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በውይይታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት እንዲሁም በደቡብ ደቡብ ማዕቀፍ በባለብዙ መድረኮች ትብብራቸውን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል።
ኤልሳልቫዶር በአፍሪካ ሁለተኛ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ለመክፍት መወሰኗን የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የገለፁ ሲሆን በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደማይላቸው አምባሳደር ታዬ ለሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ አገሮች በቀጣይ የፖለቲካ ምክክሮች ለማድረግ በሚያስችሉ እንዲሁም በትምህርት በግብርና በስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብራቸውን አጠናክሮ ለመስራት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።