የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት በተነሳው የቤተ-ክርስቲያኗ ሁለገብ ሕንጻ ምትክ አዲስ ግንባታ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት በተነሳው የቤተ-ክርስቲያኗ ሁለገብ ሕንጻ ምትክ አዲስ ግንባታ አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 21/2016 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት ምክንያት በተነሳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ ምትክ አዲስ ግንባታ አስጀመረ።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኋላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ የሁለገብ ሕንጻው ግንባታ ሙሉ ወጪ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን ጠቁመው ህንጻው አንድ ቤዝመንት ያለውና ባለ አራት ወለል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ሕንጻ በሁለቱ አካላት ስምምነት በኮሪደር ልማት ምክንያት መፍረሱን ገልጸው አሁን ላይ የአከባቢውን ልማት በሚመጥን መልኩ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ህንጻውን በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለቤተ-ክርስቲያኗ የሚያስረክብ ይሆናል ተብሏል።
ግንባታው በፍጥነት፣ በጥራት እና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ከተማዋን ለማስዋብ የሚደረጉ ስራዎች የሚያስደስቱ ናቸው ብለዋል።
በመልሶ ማልማት ምክንያት የፈረሰውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ወጪ መልሶ ገንብቶ ለማስረከብ መወሰኑን አድንቀዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው ልማቱ በሁሉም ዘንድ የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ ከመልሶ ማልማት ስራው ጎን መሆኗን ጠቁመው ለተደረገው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዛሬው ዕለት ግንባታው የተጀመረው ሕንጻ በተለምዶ የመሃሙድ ሙዚቃ ቤት ተብሎ ሲጠራ የነበረው የቤተክርስቲያኗ ይዞታ ነው።