ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ የተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉ ተገለፀ    

ድሬዳዋ ፤ሚያዝያ 21/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ስራ መመለሳቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

"ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሐሳብ በድሬዳዋ  የሶስተኛው ዙር ንቅናቄ  ከነገ ጀምሮ በይፋ ይጀመራል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ንቅናቄውን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አብዲ በመግለጫቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በአስተዳደሩ በተካሄደው ንቅናቄ እና በተደረገው ዘርፉ ብዙ ድጋፍ ስድስት የተዘጉ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተመልሰው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ነው ያወሱት።

" ፋብሪካዎቹ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ አድነዋል፤ ከሶስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥረዋል" ብለዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ በንቅናቄው ዘመቻ ለመዘጋት ጫፍ ላይ የደረሱ ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ስራ ተመልሰዋል ብለዋል።

በሚደረገው ድጋፍና ክትትል የተበረታቱ አዳዲስ ባለሃብቶችም ወደ ኢንቨስትመንት ስራ በብዛት እንዲሰማሩ መደላደል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

እነዚህን አበረታች ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከነገ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚዘልቅ የሶስተኛው ዙር "የኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" ንቅናቄና ኤክስፖ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በንቅናቄውና በንግድ ኤክስፖው ከ42 እስከ 45 የሚሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው በተደረገላቸው ድጋፍ እያመረቱ የሚገኙትን ተኪ ምርቶች የሚያቀርቡ ሲሆን  በኢንዱስትሪዎች  ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችም እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል።

በዝግጅቱ ላይ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተደረጉ ጥናቶች ላይ ውይይት እንደሚደረግና አምስት አዳዲስ ፋብሪካዎች በይፋ ተመርቀው ወደ ስራ እንደሚገቡም አስታውቀዋል።

ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ዝግጅት ላይ የፌደራልና  የዘርፉ ከፍተኛ የአመራር አባላት እንዲሁም የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የዘርፉ ኃላፊዎች በዝግጅቱ ላይ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም