የመንግስት ተቋማትን የዲጂታል አቅም በማጎልበት ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ የመንግስት ተቋማትን የዲጂታል አቅም በማጎልበት ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተቋቋመው የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የስራ እንቅስቃሴ  ተመልክቷል።

ቡድኑ የአይ ሲ ቲ ፓርክ፣ የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከልና የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት የኮቪድና የሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የመድሃኒት ምርምር የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሱፐርቪዥን አካሂደዋል።

የሱፐርቪዥን አስተባባሪ ተገኔ ኃይሉ በዚሁ ወቅት ስታርትአፖችን በአይሲቲ ፓርክ በማስገባት የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራው እንዲጎለብት እየተከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ልዩ ተሠጥኦ ያላቸው ተዳጊዎች ክህሎት ለማጎልበት የተሰጠውን ትኩረት አድንቀው፤ ከዚህ አኳያ በተለይ  የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከል በተሟላ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም አገልግሎታቸውን በዲጂታል ስርዓት(ኢ-ሰርቪስ) ተደራሽ ማድረግ ከሚጠበቅባቸው  64 ተቋማት ውስጥ 25 ብቻ እየሠጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ የመንግስት ተቋማትን የዲጂታል አቅም በማጎልበት ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

አገልግሎታቸውን በዲጂታል ስርዓት ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ ተቋማትን ማገዝና መደገፍ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ በቡራዩ ማዕከል ልዩ ተሠጥኦ ያላቸውን ወጣቶች አቅም በማጎልበት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የቡራዩ ማዕከል በቂ ባለመሆኑ የሳይንስ ካፌዎችንና መሰል ስራዎችን በማስፋት የታዳጊዎችን ተሰጥኦ ለማጎልበት ስራዎች መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ጭምር የታዳጊዎችን ተሰጥኦ ለማበልጸግ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ተቋማት ዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ቅንጅታዊ አሰራርን የተከተለ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ነው ያብራሩት፡፡


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው 10 ሺህ ለሚሆኑ ባለ ተሰጥኦ ወጣቶች በቡራዩ የተሠጥኦ ማበልጸጊያ ማእከል ስልጠና እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ከተያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም