ቀጥታ፡

ከምርምር ማዕከላት የሚፈልቁ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተግተው ሊስሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ ከምርምር ማዕከላት የሚፈልቁ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተግተው ሊስሩ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትሩ( ዶ/ር )ግርማ አመንቴ አሳሰቡ።

የግብርና ሚኒስትሩ በመልካሳ ምርምር ማዕከል ተገኝተው በአትክልትና ፍራፍሬ ሜካናይዜሽን እየተሰሩ ያሉ የምርምር ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በስንዴ ላይ ያሳየውን ስኬት በአትክልትና ፍራፍሬ ሊደገም  ይገባል ብለዋል።

መልካሳ ግብርና ምርምር እንደሀገር በአትክልትና ፍራፍሬ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።


 

ቴክኖሎጂ ማፍለቅ ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት (ዶ/ር) ግርማ በምርምር ማዕከላት የተገኙ ምርምሮችን በማባዛት ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በምግብና ስርዓተ ምግብ ራስን ለመቻል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአትክልትና ፍራፍሬዎች  ምርትን  በሰፊው በማልማት ከምግብነት ባሻገር ለኤክስፖርት ለማቅረብ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) የምርምር ማዕከላት ቴክኖሎጂ የማፍለቅ፥ ማስተዋወቅ፥ ተደራሽ ማድረግና አቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቋቋመ 60 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ምርምር ማዕከል 2000 አዳዲስ የምርምር ዝርያዎችን እየሰራ መሆኑን ዶ/ር ፈቶ ጠቁመዋል፡፡

በባህላዊ መንገድ ከ5-10 የፍራፍሬ ችግኝ የሚባዛውን በTissue Culture እስከ 2 ሺ ችግኝ ማግኘት መቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ  መግለጸቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም