የብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ግብርና ምርታማነት በማስቀጠል የዘርፉን  ኢንቨስትመንት ያሳድጋል

79

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ የብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ግብርና ምርታማነት በማስቀጠል በዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት እንዲያድግ መልካም ዕድል እንደሚፈጥር የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በግብርና ምርታማነት እምርታዊ ዕድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በግብርና መስክ እየተመዘገበ በሚገኘው ዕድገትም ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥምረት በወጪና ገቢ ምርት የንግድ መዳረሻዋን በማስፋት ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል።

በቡና፣ አበባ፣ የሙዝና አቮካዶ ፍራፍሬ ወጪ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ የወጪ ንግድ መዳረሻ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የግብርና ግብዓቶችን ለማስገባት ና የኢትዮጵያን  ምርቶች  በቀላሉ ለመቀያየር እንደሚረዳም አንስተዋል።

የብሪክስ ጥምረት አባል ሀገራት በኢትዮጵያ የግብርና መስክ የሚኖራቸውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብ ትልቅ ዕድል ማምጣቱን ተናግረዋል።

የጥምረቱን አባል ሀገራት የቴክኖሎጂ፣ ሳይንስና የፈጠራ ሽግግርን በማሳለጥ የግብርና ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ለኢትዮጵያ የተሻለ እድል ነው ብለዋል። 

በሰው ሃይል በኩልም ኢትዮጵያዊያን በጥምረቱ አባል ሀገራት የስራ ዕድል የሚያገኙበት እና ተሞክሮን የሚቀስሙበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

በቅርቡ የኢትዮ-ሩሲያ የጥናትና ምርምር የባለሙያዎች ቡድን ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በብሪክስ ማዕቀፍ ስር ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል መድረክ በአዲስ አበባ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም