አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል-የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን 

109

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።  

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍና ተደራሽነትን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እየቀረበ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሰብአዊ ድጋፉ በየሩብ ዓመቱ እንደሚሰራጭ ጠቅሰው ከጥር እስከ መጋቢት ድረስ ለ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

አሁን ባለንበት ወቅትም ከሚያዝያ አንስቶ እስከ ሰኔ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ በመንግስትና  በአጋር አካላት ትብብር እንደሚከናወንም እንዲሁ።

በአጠቃላይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ላለው ድጋፍ 11 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጭ የሚጠይቅ  ሲሆን  5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ በመንግስት ይሸፈናል ነው ያሉት፡፡

ቀሪው በለጋሽ አካላት እንደሚሸፈንም ነው የተናገሩት፡፡

የመንግስት ዋነኛ ትኩረት አደጋን ቀድሞ መከላከል መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለዚህም የተጋላጭነት ልየታ የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል ጥናት መሰራቱን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ወረዳዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ ጥናት መሸፈናቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም