የኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ ስብት ማዕከልነት እየጨመረ መጥቷል

158

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ ስብት ማዕከልነት እየጨመረ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

ስብሰባው "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት" በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወሳል።


የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ ስብት ማዕከልነቷ እየጨመረ መጥቷል።

የሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ ላይ በተሰራ ስራና ቀደም ሲል በነበራት አኩሪ ታሪክ በዓለም የዲፕሎማሲ ስብት ማዕከልነቷ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና አንድነት ላበረከተችው አስተዋጽኦ የአፍሪካ መዲና ለመሆን በቅታለች።

 

የቀደሙ የኢትዮጵያ መሪዎች በሰሩት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ የሕብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ሊሆን ችሏል ብለዋል።

የተወሰኑ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት የሕብረቱን መቀመጫ ወደ ሌላ ሀገር ለማዛወር ያደረጉት ጥረት በኢትዮጵያ መሪዎች ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ሳይሳካ መቅረቱን አስታውሰዋል።

 

በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅና የኢትዮጵያ ከፍታ እንዲጨምር ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የበለጠ በቅንጅት በመስራት እንግዳ ተቀባይነታችንን ለዓለም እያስመሰከርን መቀጠል አለብን ብለዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ጊዜ፤ 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በከፍተኛ ቅንጅት በስኬት መጠናቀቁን አስታውሰዋል።

በሕብረቱ ስብሰባ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶች ተሳትፈው በሰላም ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል።

ለዚህም የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ስብሰባው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም