በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ 112 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል

84

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ 112 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የተመራ ቡድን በተለያዩ ወረዳዎች በበልግ እርሻ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እየተመለከተ ነው።

በጉብኝቱ ላይ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና ወረዳ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በቦርቻ ወረዳ ፍላሳ ቀበሌ በክላስተር የለማ የበቆሎ ማሳን በጎበኙበት ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎች የክልሉ አመራር አባላት የኩትኳቶ ስራ በማከናወን ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን አበረታተዋል።

የሲዳማ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ባንጉ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉብኝቱ የበልግ እርሻ ልማት ያለበትን ደረጃ ለመቃኘት ያለመ ነው።

በክልሉ በበልግ እርሻ 112 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ ከ68 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት በዋና ዋና ሰብሎች መልማቱን ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በ25ሺህ 284 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ በኩታ ገጠም መልማቱን አስረድተዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት የተስተካከለ የበልግ ዝናብ ስርጭት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ባንጉ፣ በዘር ከተሸፈነው መሬትም 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው በኩታ ገጠም ልማት ተመሳሳይ ሰብል ማልማታቸው የተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በተያዘው የበልግ እርሻም በኩታ ገጠም ያለሙት የበቆሎ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከዚህም በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የመስክ ምልከታው በቀጣይም በሎካ አባያ እና ብላቴ ዙሪያ ወረዳዎች እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም