በአማራ ክልል ከ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቡናና ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ

65

ደሴ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የሚተከሉ ከ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቡናና ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ቡናና ፍራፍሬን ጨምሮ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የተለያዩ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።

ቢሮው በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በክልሉ ለሚተከለው የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ቅደመ ዝግጅት የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በክልሉ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲለሙ ብሎም የደን ሽፋንን ለማሳደግ እየረዳ ይገኛል።

እንዲሁም አርሶ አደሩ ከቡናና ፍራፍሬ ልማት ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ አቅሙ እንዲጠናከር በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ለማጠናከር ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የሚተከሉ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የተለያዩ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሚተከሉት ችግኞች 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቡናና ፍራፍሬ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ቃልኪዳን፤ እስካሁንም ከ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቡናና ፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የቡናና የፍሬፍሬ ችግኞቹ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በተከናወነባቸው ተፋሰሶች እና በአርሶ አደሩ ማሳ እንደሚተከሉ ጠቁመው፣ ለዚህም ከ3ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት መለየቱን አስተውቀዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አሳልፍ አህመድ በበኩላቸው፣ በዞኑ በቡናና ፍራፍሬ ልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ባለፉት ዓመታት ከ6ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቋሚ ፍራፍሬ መልማቱን አውስተው፤ ከዚህ የሚገኘው ምርት ከአካባቢው ተርፎ ሌሎች አካባቢዎች ገበያ እየቀረበ ነው ብለዋል።

በዞኑ ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ቡድን መሪው ያመለከቱት።

የቡናና ፍራፍሬ ልማት በክላስተር ጭምር በመጀመሩ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ ነው ያሉት ደግሞ በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ተወካይ አቶ ቦጋለ መንግስቱ ናቸው።

በዞኑ በቀጣዩ የክረምት ወቅት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር የተለያዩ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም