በጋምቤላ ክልል ገቢን በማሳደግና በጀትን በአግባቡ በመጠቀም ለልማት ዕቅዶች ውጤታማነት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ

72

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የገቢ አቅምን በማሳደግና በጀትን በአግባቡ በመጠቀም የልማት ዕቅዶችን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ። 

ክልል አቀፍ የፋይናንስና የገቢ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለውን ውስን በጀት በአግባቡ በመጠቀምና የገቢ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል። 

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ያለውን በጀት ሁለንተናዊ ዕድገትን በሚያመጡ የልማት ዘርፎች ላይ ለማዋል በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል። 

የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግም የገቢ አሰባሰብ ስርዓት፣ የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ማሻሻያዎች ሲተገበሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኡሞድ፣ በዘርፉም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። 


 

ሆኖም በጀትን በአግባቡ ባለመጠቀምና ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ያለመሰብሰብ ችግሮች በየዓመቱ ለበጀት ጉድለት ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከአደረጃጀትና ከመዋቅር መስፋት ጋር ተያይዞ የሚደረግ የሰው ሃይል ቅጥርና ምደባ ለበጀት ጉድለት መንስኤ መሆናቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቀሱት። 

የበጀት አጠቃቀምንና የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ይበልጥ በማዘመንና በማሻሻል የታለሙ የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። 


 

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው በበኩላቸው በክልሉ በየዓመቱ የሚመደበውን በጀት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ዘርፎች በማዋል የህዝቡን መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

በክልሉ የሚሰበሰበው ገቢ በየዓመቱ እየተሻሻለ መምጣቱንም ተናግረዋል። 

ያለውን በጀት በአግባቡ ልማት ላይ በማዋል በኩል የሚታዩ ውስንነቶችን በማስተካከል የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም