ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

143

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2016(ኢዜአ)፡- ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሀገረ መንግስት ግንባታው ውጤታማ እንዲሆን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሴቶችን ተሳትፎ ለማጉላት "አገራዊ ምክክር ለአንቺ፤ ስለኢትዮጵያ በአንቺ፤ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በብሔራዊ ምክክር ያለፉ አገራት በጦርነት ከሚገኝ ጊዜያዊ መፍትሔ ይልቅ ለንግግርና ምክክር ቅድሚያ በመስጠታቸው ዘላቂ ሰላምን በመፍጠር የተሻለ ኢኮኖሚ እየገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የተሻለ ሀገር ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ስላለው ሴቶች ገንቢ ተሳትፏቸውን ለማበርከት መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው አስገንዝብዋል።

በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ሴቶች ግንባር ቀደም የጉዳት ሰለባ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለዚህም በሀገረ መንግስት ግንባታ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ወሳኝ ተሳትፏቸውን ማጉላት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ስልታዊ መፍትሔን በማበጀት ረገድ ሴቶች የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ፀጋ የላቀ በመሆኑ ምክክሩ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አብራርተዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሴቶች ድምፅ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው በማመን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም