በዕቅድ መመራት ካልቻልን ለህዝቡ የገባነውን ቃል ማሳካት አንችልም - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

141

አዳማ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦በዕቅድ መመራት ካልቻልን ለህዝቡ  የገባነውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ቃል አናሳካም ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በክልል ያለፉት ዘጠኝ ወራት የመንግሥትና የፓርቲ የስራ አፈፃፀም ክንውንና የ2017 ዓ.ም መነሻ ዕቅድ ላይ ያተኮረ ግምገማ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።

በመድረኩ ላይም አቶ ሽመልስ እንደገለጹት በዕቅድ መመራት ካልተቻለ ለህዝቡ የተገባውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

እቅዱ የሚሳካው በተሰጠው አቅጣጫ በአግባቡ ሲተገበር መሆኑን ገልጸው ከዚህ አኳያ የተሰጠ አቅጣጫ ቆጥሮ በመቀበል ያለመተግበር ክፍተቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የልማት፤ የሰላም፣ የአገልግሎትና መልካም አስተዳደር ውጤቶች የምዘና ዝንባሌ በትንሽ ድሎች መዘናጋት እየፈጠረ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ከዚህ  አስተሳሰብና ተግባር መውጣት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

የ2017 ዓ.ም ዕቅድም በዚህ መልኩ መፈፀም እንደማይቻል ገልጸው መድረኩ አመራሩ የእቅዱን ማስፈፀሚያ ስልቶች በሚገባ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው መድረኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለህዝቡ የተገባውን ቃል እውን ከማድረግ አኳያ የታዩ ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በየአካባቢው የሚገኙትን አቅሞችና አማራጮች በመለየት ለዕቅዱ ውጤታማነት የምንጠቀምበት ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ፓርቲው ለህዝቡ የገባውን ቃል ከማሳካት፣ ጽንፈኝነትን ከመታገልና አስተማማኝ ሰላም ከማስፈን እንዲሁም የተዛቡ አመለካከቶችን ከማረም ጀምሮ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የሚሰራበት መሆኑንም አስረድተዋል።


 

ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና መፍጠር ውስጣዊ ትግላችንን ማጠናከር ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ ሰላምን ማስፈን ፣ልማትና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የሚፈትሽበት ነው ብለዋል።

መድረኩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የመንግስትና የፓርቲ ስራ ክንውን፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የ2017 ዓ.ም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስፈፀሚያ የመነሻ ዕቅድ ቀርቦ ምክክር ይካሄድበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም