የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ

88

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተጓዦችና የጭነት አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን  አስታወቀ።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማኅበሩ መንገደኞችንና ጭነትን የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

ማኅበሩም በየቀኑ ከ700 እስከ 1ሺህ ሰዎችን በማጓጓዝ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለጠንካራ ቀጣናዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ትስስር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በሁለቱም ሀገራት የሰበታና ሆልሆልን ጨምሮ አዳዲስ የባቡር መዳረሻዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሠረተ-ልማት መገንባት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የባቡሩ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ በጀመረባቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት ጊዜ በየዓመቱ ከ35 እስከ 41 በመቶ የሚደርስ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ155 ሺህ በላይ ተጓዦችን እና 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የጭነት አገልግሎት በማጓጓዝ የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰጠው ተጓዞችንና ጭነት የማጓጓዝ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ባለቤትነት የሁለቱ ሀገራት መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመርም ሀገራቱ የጋራ ተጠቃሚነት ዓላማ በማስቀመጥ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም በኩል የተሳለጠ የወጪና ገቢ ምርት የሎጂስቲክስ አገልግሎት በመስጠት የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማሳለጥ ዓላማ አድርጎ የተገነባ መሠረተ-ልማት መሆኑን ገልፀዋል።

በግብርና መስክ የቁም እንስሳት፣ የቡና እና የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የማዕድንና ኢንዱስትሪ ወጪና ገቢ ምርት በማጓጓዝ ለኢኮኖሚ ዕድገት መሳለጥ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርን የማስተዳደር፣ የመጠገንና የመከታተል ሥራ በውጭ አገር ኮንትራክተር ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።

ከ13 እስከ 15 በመቶ የወጪና ገቢ ምርት የሚያጓጉዘውን ማኅበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2024 ጥር ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች መሆኗን ገልፀዋል።

በባቡር ትራንስፖርት ምቹ ምኅዳር በመፍጠርም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የገቢና ወጪ ምርት የማጓጓዝ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ ከ1ሺህ በላይ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በማጓጓዝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት እየደገፉ እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት የሁለቱን አገራት ዜጎች በማገናኘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም