የአማራ ክልል ከፍተኛ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ጋር ምክክር አደረገ

150

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016 (ኢዜአ)፡- ወደ ሰሜን አሜሪካ የሥራ ጉዞ ያደረገው የአማራ ክልል ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ጋር ምክክር አደረገ።

ልዑኩ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመዘዋወር ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከልዩ ልዩ ኩባንያዎች፣ ከዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማትና አካላት ጋር ውይይት እና ምክክር አድርጓል።

በዋሽንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር የተደረገው ውይይት ደግሞ መንግሥትና ኤምባሲው ማከናወን ስለሚገባቸው ቀጣይ ሥራዎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል።


 

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እና ዲፕሎማቶች ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረጉት ምክክር፥ የተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደነበር ገልጸው፤ በቀጣይም ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስገኘት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት እንደ መነሻ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ እና በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኅላፊ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም እንዲሁም ወቅታዊ የሀገሪቱን እና የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ ለዲፕሎማቶች መረጃ እና ማብራሪያ ሰጥዋል።

የልዑካን ቡድኑ በአሜሪካ በነበረው ቆይታ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን ማከናወኑን አውስተው በቀጣይ ከዚህ ጉዞ የተገኙት ተሞክሮዎች ተቀምረው ከትውልደ- ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራውን ከዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም